Address
Addis Ababa

Work Hours
Monday to Saturday: 8AM - 5PM

“በኢትዮጵያ የተመረተ” የሚል መኪና የመስራት ህልሙን ያሳካው ኢትዮጵያዊ

ወጣቱ የፈጠራ ባለሙያና ስራ ፈጣሪ ሺሃብ ሱሌይማን “ታይታን” ሲል የሰየማትን መኪና ሰርቶ ለእታ አቅርቧል

አል-ዐይን

2021/8/16 13:23 GMT

8 ሰው የመጫን አቅም ያላት መኪናዋ የትራንስፖርት ችግርን ለመቅረፍ እንዲሁም ለሰርግና ለመዝኛኛ ታልማ የተሰራች ነች

ወጣቱ የፈጠራ ባለሙያ ሺሃብ ሱሌይማን ይባላል። በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የኮምፒውተር ሳይንስ 2ኛ ዓመት ተማሪ ነው።

የፈጠራ ስራዎችን ገና የ5ኛ ክፍል ተማሪ እያለ መስራት መጀመሩን የሚናገረው ሺሃብ በመጫዎቻዎቹ ላይ ያይ የነበረው ‘ሜድ ኢን ቻይና’ የሚል ጽሁፍ፤ ለምን ‘ሜድ ኢን ኢትዮጵያ’ የሚል አልሆነም በሚል ሃገር በቀል የፈጠራ ስራዎችን ለመስራት እንዳነሳሳው ይናገራል።

መኪና የመስራት እቅዱ ያኔ እንደተወለደ የሚናገረው ሺሃብ፤ አሁን “ታይታን” ሲል የሰየማትንና ከሰሞኑ ለዕይታ የበቃችውን ባለ አራት ጎማ መኪና በራሱ አዲስ ንድፍ (ዲዛይን) ሰርቷል።

ሺሃብ ከፕላኔቶች ሁሉ ለሳተርን አለኝ በሚለው ልዩ ፍቅር ምክንያት መኪናዋን በትልቁ የሳተርን ጨረቃ ስም “ታይታን” ሲል መሰየሙንም ከአል ዐይን አማርኛ ጋር በነበረው ቆይታ ገልጿል።

“ታይታን” በባለሶስት እግር እና በሚኒባስ መካከል የምትገኝ መኪና ነች። በአንድ ጊዜም ስምንት ሰዎችን የመጫን አቅም አላት። ኢትዮጵያ ውስጥ አለመመረቱን ተከትሎ የመኪናዋ ሞተር ከውጭ መጥቶ ነው የተገጠመው። ከሞተሩ ውጪ ያሉ ሻንሲና መሰል ቀሪ የመኪናዋ አካል ክፍሎች ግን በአገር ውስጥ ከሚገኙ ግብአቶች የተዘጋጁ ናቸው። ለዚህም ሺሃብ የተለያዩ የአልሙኒየም፣ የፋይበር ማይካ እና የብረት ግብዓቶች ተጠቅሟል።

የመኪናዋ “ዳሽ ቦርድ” ‘ስማርት ዲስፕሌይ’ የተገጠመለት ነው። ይህም ስልክ ለማንሳት፣ ሙዚቃ ለማጫወት፣ እንዲሁም ኮምፓስ እና አቅጣጫ ለመመልከት (ማፕ) ለመጠቀም ያስችላል እንደ ሺሃብ ገለጻ።

ናፍጣን በነዳጅ ግብዓትነት የምትጠቀመው “ታይታን” ለረጅም ሰዓት በአግባቡ ከማገልገልና ከአዋጭነት አንጻር ታይቶ የህዝብ ትራንስፖርትን ታሳቢ በማድረግ የተሰራች ናት፡፡ ወደ ፊት አዋጭነቱ እየታየ በፀሃይ ሀይል (ሶላር) እና በኤሌክትሪክ ልትሰራ በምትችልባቸው መንገዶች ዙሪያ እንደሚሰራም ተናግሯል።

“ታይታን” በተለይም በአዲስ አበባ ከተማ ያለውን የትራንስፖርት ችግር ለመቅረፍ ትረዳለች የሚለው ሺሃብ ለመዝናናት እና ለሠርግ የሚሆኑ ተጨማሪ ግልጋሎቶችንም ታሳቢ አድርጋ የተሰራች ነች ይላል።

የመኪናዋ ናሙና (ሳምፕል) ከባለሃብቶች ጋር በመነጋገር መሰራቱንም ነው፤ በቅርብ ጊዜ ውስጥም በስፋት ወደ ማምረት እንዲገባ ከስምምነት ላይ ተደርሷል ነው የሚለው ሺሃብ።

“ታይታን፤ በአዲስ አበባ ጎዳናዎች ላይ የምትታይበት ጊዜ ሩቅ አይደለም” ሲልም ይናገራል ወጣቱ የፈጠራ ባለቤት።

ሺሃብ ከታይታን ውጭ በአምስት የተለያዩ ዘርፎች ማለትም በኤሌክትሮኒክስ፣ በአውቶሞቲቭ፣ በሮቦቲክስ፣ በአርተፊሻል ኢንተለጀንስ፣ በስፔስ እንዲሁም በበይነ መረብ (ኢንተርኔት) ላይ ያተኮሩ የፈጠራ ስራዎችን መስራቱንም ለአል ዐይን አማርኛ ተናግሯል።

የመጀመሪያ የፈጠራ ሥራው የኤሌክትሪክ ማብሰያ ምድጃ (ስቶቭ) ነው፡፡ የዳቦ ማሽን፣ ስማርት ረከቦት፣ ስማርት አልጋ በርን በይለፍ ቃል መዝጋት እና መክፈት የሚያስችሉ የፈጠራ ስራዎችንም ሰርቷል።

የራሱን ድርጅት ባቋቋመበት የሮቦቲክስ የፈጠራ ስራ እስከ ሕንድ ድረስ በመጓዝ መወዳደር መቻሉንም ተናግሯል ሺሃብ።

በእነዚህ ሥራዎቹ አማካይነትም ከቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ እንዲሁም ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ እጅ ሽልማት አግኝቷል።

በአሁኑ ወቅትም “ኤን ሶፍት” የሚል ድርጅት አቋቁሞ መተግበሪያዎችን በማበልፀግ ለድርጅቶች እያቀረበ መሆኑንም ነው በዚህ ዘርፍም ስኬታማ ነኝ የሚለው ሺሃብ የሚናገረው።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *